Donderdag 04 Julie 2019

Sidama region

የፊታችን ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓም የሲዳማ ሕዝብ ደቡብ ከሚባል ድሪቶ ውስጥ ለማደር የማይገደድበት እና በራሱ ዕጣ ፈንታ ላይ በራሱ ምክር ቤት ራሱ ብቻ የወሰነበትን ውሳኔ የሚያጸናበት ቀን ነው ሲል ኤጄቶ የተባለው የሲዳማ የመብት አቀንቃኝ ቡደን አስታወቀ። ቡድኑ ዛሬ በሐዋሳ ከተማ ከአባላቱ እና ከደጋፊዎቹ ጋር መወያየቱን በመግለፅ የሲዳማ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ዙሪያ ያለውን አቋም በማኅበራዊ ድረ ገጹ ይፋ አድርጓል። በዚሁ መግለጫው አንዳመለከተው የሲዳማ ኤጄቶች የሲዳማ ጥያቄ እና ጥያቄው የሚፈታበት ዴሞክራሲያዊ መንገድ ሀገራዊ ለውጡን በማይናድ መሠረት ላይ የሚገነባና ኅብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝሙን የሚያጠናክር ኩነት መሆኑን እናምናለን ብሏል። የሲዳማ ክልል ጥያቄን አስመልክቶ ከየትኛውም አካል የሚሰጥ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ፡ ምላሽ ምንም አይነት ተቀባይነት አይኖረውም ያለው መግለጫው ጥያቄያችንን እና ውሳኔያችንን ለመቀልበስ የሚነዙ ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎች የሲዳማን ሕዝብ ጥንታዊ የጀግንነት ስነልቦና በጉልህ ካለመገንዘብ የሚመነጩ ተራ ፉከራዎች እንደሆኑ እንገነዘባለን ሲልም አትቷል። የሲዳማን ሕዝብ የነጻነት ቀን ለማጨለም እና ሃሳቡንም በተንሸዋረረ መልኩ የተረዱ አካላት ይህን ቀን የዓለም ፍጸሜ በማስመሰል የሚያሰሙትን ተራ ፕሮፓጋንዳ አምርረን እንቃወማለን ሲል መግለፁን ከሐዋሳ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሰኞ ለአገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት ዓመታዊ የሥራ ዘገባ ባቀረቡት ወቅት ሲዳማን ጨምሮ በክልል ለመደራጀት ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖች ለጥያቄያቸው ምላሽ እስኪሰጥ በትዕግስት እንዲጠብቁ ጠይቀዋል። ከዚህ ውጭ በኃይል እና በደቦ ለማስፈጸም የሚሞክሩ አከላት ካሉ መንግሥታቸው ሕግ ለማስከበር ወደኋላ እንደማይል ማስጠንቀቂያ አዘል የሚመስል ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለም ኢትዮጵያ ውስጥ በየክልሉ የሚታዩ ሽኩቻዎች የሀገሪቱን አለመረጋጋት እንዳያባብሱት ዓለም አቀፉ የቀውስ አጥኚ ቡድን አሳሰበ። ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ የሲዳማ ሕዝብ መሪዎች ለጥያቄያቸው የፌደራል መንግሥትን አዎንታዊ ምላሽ ካላገኙ ከፊል ራስገዝ አስተዳደርነትን በመጪው ሐምሌ አጋማሽ ለማወጅ መዘጋጀታቸውን አሳውቀዋል። ለተባለው ወሳኝ ቀን የሁለት ሳምንታት ዕድሜ ቢቀርም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሕዝበ ውሳኔ እንዲሰጥበት ቀን እንዳልቆረጡ እና ዝግጅትም እንዳላደረጉ ቡድኑ ይፋ ባደረገው ዝርዝር ዘገባ ጠቅሷል። ጉዳዩ በአግባቡ ካልተያዘ በሲዳማ በኩል የሚታየው ፍላጎት አመፅን በማቀጣጠል የሀገሪቱ ጥምር መሪ ፓርቲ የገጠመውን ቀውስ ሊያባብስ እንደሚችል ክራይስስ ግሩፕ አመልክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢል አህመድ እና የግንባሩ መሪዎች ከሲዳማ ሕዝብ መሪዎች ጋር የሚግባቡበትን መንገድ እንዲፈልጉ እና ቆየት ብለውም ለሕዝበ ውሳኔው ቀን መቁረጥ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።

Geen opmerkings nie:

Plaas 'n opmerking

GMN/lOTOONNI PP WBO-TTI MKAMAN